LOADING...

GTV

Trending Today
 የዕለቱ ዜናዎች
March 28, 2024

የዕለቱ ዜናዎች

By
የዐብይ አሕመድ አገዛዝ በተለያዩ ሚዲያዎች የሚሰሩ ጋዜጠኞችንና የማህረሰብ አንቂዎችን ለመክሰስ በዝግጅት ላይ መሆኑን የግዮን ቴሌቪዥን ምንጮች ገለጹ። አገዛዙ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ጋዜጠኞችንና የማህበረስብ አንቂዎችን ለመክሰስ መረጃዎችን እያሰባሰበና የሀስት ክስ እያዘጋጀ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። በዐብይ አህመድ ትዕዛዝ ክሱን እንዲያዘጋጁ መመሪያ የተሰጣቸው የመንግስት አካላት የኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤትና የፌዴራል ፍትህ ሚንስቴር መሆናቸውም ታውቋል። በዚሁ ክስ የሚካተቱ ጋዘጠኞችና የማህበረሰብ አንቂዎች ስም ዝርዝር በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ተብሏል። ጋዜጠኞቹና የማህበረሰብ አንቂዎቹ ከፋኖ ጋር በመተሳሰር የትጥቅ ትግል ይደግፋሉ፥ የሽብር ጥቃት እንዲፈጸም ያስተባብራሉ በሚል ክሱ እየተዘጋጀ ነው ተብሏል። የአገዛዙ መሪ 0ብይ አህመድ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የሚዲያ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች ጋር ውይይት በቅርቡ ለማካሄድ ዕቅድ መያዙን የጠቆመው ምንጫችን ከዚህ በኋላ ተለይተው በተመረጡት ላይ ግን ጠበቅ ያለ ክስ እንደሚመሰረትባቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። የአብይ አህመድ አገዛዝ የጋዜጠኞችን ክስ የሚከታተልና የሚያጠና ኮሚቴ ቀደም ብሎ በማቋቋም ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱንም የግዮን ቴሌቪዥን ምንጭ ገልጿል። ===========/// ============= ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ስልጣን ከያዘ ወዲህ በእስር ላይ በሚገኙ ሰዎች ላይ ከባድ ኢሰብዓዊ ጥሰቶች እየተፈፀመ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት ገለጸ። በታሳሪዎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጭካኔ የተሞላበት ማሰቃየት ተግባር ለከፍተኛ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት እንደዳረጋቸውና ጉዳዩም እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታውቋል፡፡ ይህ ኢሰብዓዊ የእስረኞች አያያዝ በአማራ፣ በደቡብ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በሚገኙ ታሳሪዎች ላይ እየተፈፀመ መሆኑን ሪፖርቱ አጋልጧል :: የዘፈቀደ እስር፣ ከሕግ አማካሪ ጋር መገናኘትን መከልከል፣ የቤተሰብ ጉብኝት ክልከላ እና የመሳሰሉት በታሳሪዎች ላይ ከሚፈፀሙት የመብት ጥሰቶች ጥቂቶች እንደሆኑም በሪፖርቱ ተመልክቷል። በፖሊስ እየተፈጸመ ያለው ‹‹የምትክ እስራት›› ወይም ተጠርጣሪው እስከሚገኝ የቤተሰብ አባልን የማሰር ዕርምጃ፣ ከእነዚህ የመብት ጥሰቶች አንዱ እና አሳሳቢ ድርጊት እንደሆነም ተጠቁማል። በተጨማሪም በአማራ ክልል ፖለቲካዊ ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎች ለዘፈቀደ እስራትና ለተያያዥ የመብት ጥሰቶች ተጋልጠዋል ነው የተባለው። በአሁኑ ወቅት በርካታ ዜጎች ሐሳባቸውን በነፃነት በመግለፃቸው እና ሰላማዊ የፖለቲካ ተሳትፎ በማድረጋቸው ብቻ የሚታሰሩ በርካታ መሆናቸውንም ኢሰመኮን ጠቅሶ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል። ==============///================ በሜጀር ጄኔራል ውብአንተ አባተ መሰዋት አርበኛው የቆመለትን ዓላማና ራዕይ ከዳር ለማድረስ የበኩሉን የትግል አስተዋፅዖ በቁርጠኝነት እፈጽማለሁ ሲል የዐማራ ትግል የጋራ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ። ምክርቤቱ የአርበኛ ውብዓንተ አባተ የጀግንነት መስዋዕትነት የዐማራን የህልውና ትግል ከፍ አድርጎታል ብሏል። ምክር ቤቱ በመግለጫው እንደጠቀሰው አርበኛ ውብአንተ ለነፃነት፣ ለፍትህ፣ ለእውነትና ለእኩልነት ሲታገል ውድ ሕይወቱን የሰጠ የጦር ሜዳ ጀግና ነበር። ጄኔራል ውባንተ ህዝባችን ያለበትን የህልውና አደጋ ለመከላከል ግንባር ቀደም ሆኖ በመዝመትና በጀግንነት ከጠላት ጋር ሲዋደቅ ኖሮ ተሰውቷል ሲልም መግለጫው አትቷል። መግለጫው ቀጥሎም ጄኔራል ውባንተ በሺ የሚቆጠሩ ውባንተ ጀግናዎችን አስተሳስሮ፣ “አንድነት ሀይል ነው!” በሚለው መርሁ ሌሎችም ተከትለው እንዲታገሉ በማስቻሉ ለአማራ ህዝብ ትልቅ ኩራት ሆኖአል ብሏል። ምክር ቤቱ በመግለጫው እንዳለው ጄኔራል ውባንተ ቢያልፍም የተሰዋለት አላማ የሕዝብ ስለሆነ የህልውና ዘመቻው ከበፊቱ በበለጠ ተቀጣጥሎ ይቀጥላል። የጀግናው መስዋዕትነትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ውብአንተዎችን አፍርቷል ብሏል መግለጫው። የፋኖ መሪዎች የነበሯቸውን የአካሄድ ልዩነቶች ወደ ጎን በመተውና በአንድነት በመቆም የጠላትን አከርካሪ በጋራ ሰብረዋልም ነው ያለው የአማራ ትግል የጋራ መክር ቤት መግለጫ። አርበኛው ውብአንተ በወገኖቹ ላይ የሚፈፀመውን ግፍና መከራ ለማስቆም በጀግንነት ሲታገል ኖሮ በጎንደር ክፍለ ሀገር ደራ ወረዳ ልዩ ስሙ ገላውዴዎስ በሚባል አካባቢ ከጠላት በተተኮሰ የሞርታር ጥይት ሰሞኑን በክብር መሰዋቱ ይታወሳል። =============================//========================= የኢትዩጵያ ንግድ ባንክ ከደረሰብኝ ከፍተኛ ክስረት እያገገመኩ ነው አለ። ባንኩ ከተወሰደበት ጠቅላላ ገንዘብ ከ 800 ሚሊዮን ብር በላይ እንደተመለሰለት ገልጿል፡፡ ይህም ተጭበረበርኩ ከሚለው ጠቅላላ ገንዘብ 78 በመቶ የሚሆነው ነው። ቀሪውን 20% ወይም 178 ሚሊዩን ብር ደግሞ ደንበኞቹ እስኪመልሱለት እየጠበቀ እንደሆነ የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቢ ሳኖ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። የባንኩ ፕሬዝዳንት እንደተናገሩት ከ 9 ሺህ በላይ ደንበኞች ያወጡትን የራሳችው ያልሆነ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ በፍቃደኝነት መልሰዋል። 5 ሺህ የሚደርሱ ደንበኞች ደግሞ አጭበርብረው ከወሰዱት ገንዘብ የመለሱት በከፊል እንደሆነ ነው የተገለፀው:: ወደ 10 ሚሊዩን የሚጠጋ ከአምስት መቶ በላይ በሆኑ ደንበኞች የተወሰደ ተጨማሪ ገንዘብ ቢኖርም እሱን መመለስ አልተቻለም ተብሏል:: የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፋይናንስ ሰርዓቱ መዛባት ምክንያት በደንበኞች ላይ ለደረሰው ጉዳት ይፋዊ ይቅርታ ጠይቋል። ራሱን የሚተማመኑበት ባንክ እያለ የሚያስተዋውቀው ይህ ባንክ በበርካቶች ዘንድ አመኔታ ያጣው ባንክ በሚል በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገፆች እየተሳለቁበት ይገኛሉ:: =====================================//=============================== በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን የአልሸባብ ታጣቂዎች ናቸው በተባሉ ሀይሎች በፖሊሶችና በአገዛዙ ባለሥልጣናት ላይ ጥቃት መከፈታቸው ተዘገበ። ጥቃት ፈፃሚዎቹ የሸማቂ ኃይሉ አባላት የአልሸባብ ክንፍ ሳይሆኑ እይቀርም ያለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ነው። ይህ የተደራጀና የታጠቀ ቡድን በኬንያ፣ በኡጋንዳና በሶማሊያ ኃይሎች ጭምር ይደገፋል ተብሏል። ኢሰመኩ ይህንን ሪፖርት ካወጣ በኋላ ከኢትዮጵያ በኩልም ሆነ ከአልሸባብ የተሰጠ ምላሽ ሰለመኖሩ ዘገባውን ያወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ያለው ነገር የለም። በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውና በአሜሪካ ጭምር በአሸባሪነት የተፈረጀው አልሸባብ በኢትዮጵያ ጥቅሞች ላይ ጉዳት ለማድረስ በተደጋጋሚ ሲዝት መቆየቱ ይታወሳል።
Prev Post

የዐብይ አሕመድ አገዛዝ በተለያዩ ሚዲያዎች…

Next Post

የዕለቱ ዜናዎች

post-bars

Leave a Comment